
ባለንበት ዘመን ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ ቤተ ክርስቲያን ያለፈችባቸው ፈታኝ ጊዜያቶች እንዳሉ በታሪክ ወደኋላ በመሄድ ማየት ይቻላል፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከቀድሞው ዘመን ብዙ የተለየ ባይሆንም ትልቁ ጥያቄ አገልጋዮች እና በቤተ ክርስቲያን ያሉ መሪዎች ምንያክል ለዚህ እና ይሄንን ለመሰሉ ሁኔታዎች የተዘጋጁ ናቸው የሚለውን መመለስ የሚከብድ ይመስላል፤
በሐዋርያት ሥራ እንዲህ ይላል 20:28-30
ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ። እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ። ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ።
እንዲጠነቀቁ፣እንዲጠብቁ እና እውነት እንዳትጣመም ተግተው ይሰሩ ዘንድ አደራ እንዳላቸው እናያለን፤
ባለንበት ዘመን ያሉ አገልጋዮች ወይንም መሪዎች በሦስት መልኩ ከፍለን (እኔ በግሌ) ልናያቸው እንችላለን፤
- በአገልግሎት መድረክ የተሰየሙ ነገር ግን ያልዳኑ፣
እነዚህ “አገልጋዮች” ሁኔታው አጋጣሚው እድል የሰጣቸው በእንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት ላይ እንዲሰየሙ አደረጋቸው እንጂ ስፍራቸው ያልሆኑ ሰዎች ናቸው፤ (የአስቆሮቱ ይሁዳ) ከእንደነዚህ አይነቶቹ ጋር አብሮ ሊታይ ይችላል፤
በማቴዎስ ወንጌል ጌታ እንደ ተናገረው “በሰማይ ያለውን የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉትን እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚሉት፡” ሳይሆኑ ይሄም ብቻ አይደለም፤ “ማቴዎስ 7:23
በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። (ማቴ7:21-23) በእርሱ የማይታወቁ በሙያቸው አገልጋይ ሊያስብል የሚችል ማንነት ያላቸው ሰዎች በቤተ ክርስቲያን አባላት ከመሆን ወደ መድረክ ከዛም አልፈው በመሪነት ስፍራ ተቀምጠው የሚታዩበትን ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ቃል ነው፤
መርሳት የሌለብን ኢየሱስ “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም።” ብሎ ሲናገር መደረግ ያለበት የአባቱን ፈቃድ መፈጸም እንደ አማራጭ የሚታይ ሳይሆን የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን ነው፤ ይሄንን ለመፈጸም እውነተኛ የእርሱ ተከታዮች መሆናችን ለውሳኔዎቻችንም ቁልፍ እንደሆነ ማሳያ ነው፤ ያልዳኑ ሰዎች ምንም እንኳን “ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤…” (2 ጢሞቴዎስ 3:5) ቢለንም ነገር ግን “ኅይሉን ግን ክደዋል፡” ብሎ ይለናል ያስጠነቅቀናል፤ ከእነዚህን አይነት ሰዎች ደግሞ “ከእነዚህ እራቅ” ብሎ ያዘናል፤ የመጀመሪያው እንደነዚህ ያሉትን መራቅ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ፤
2. ጥሪው አላቸው ለእውነት የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል ፈቃድኛነት
የሁለተኛዎቹ ለየት የሚያደርጋቸው ጥሪው አላቸው ለእውነት የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል ፈቃድኛነት የሌላቸው ናቸው፤ የሚያዋጣውን እንጂ ነጻ የሚያወጣውን የማይመርጡ ሞያተኞች፤ እነዚህ አይነቶቹ ምክንያቶቻቸው ምንም እንኳን የተለያየ ቢሆንም ከማኅበረሰቡ የሚመጣባቸውን ተጽእኖ በመፍራት፣ ሊመጣባቸው የሚችለውን መከራ ለመሸሽ፣ አልያም ተቀባይነትን ለማግኘት ብለው እውነትን ይሸቅጣሉ፤ ጳውሎስ ግን በ ገላትያ 1፥10 “አሁን እኔ ጐሽ ለመባል የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሰኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንሁ ነበር።”
በእንደ እነዚህ አይነቶቹ ሰዎች አገልግሎት የሃሰት ትምህርት ያለምንም ችግር ይስተናገዳል ሃሰት ለሆኑ ነገሮች ታጋሾች ናቸው፤ ጎሽታን እንጂ ስለ እውነት የሚደረግ ኮሽታን (ትግል) መስማት አይፈልጉም፤ ጳውሎስ እንዳለን ሊያስደስቱ የሚጥሩት እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰዎችን ነው ፤ በአብዛኛው (በአብላጫው) ታዋቂነት ያገኙ አመለካከቶችም ይሁኑ አስተምህሮዎችን ለማስተናገድ ሲሉ እውነትን ይበርዙታል፤ ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሯቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። 2 ጢሞቴዎስ 4:3-4 ከንደዚህ ካሉቱ ሽሽ እንደሚል ልንሸሽ ይገባናል፤ ልንሄድባቸው የማይገቡ ሰፍራዎች ናቸው፤
3. ለእውነት ታማኝ የሆኑ ዝግጅቱ ያላቸው
እነዚህኞቹ ደግሞ ለእውነት ታማኝ የሆኑ ዝግጅቱ ያላቸው ጥሪያቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው እውነትን በምንም መንገድ የማትለወጥ ልንኖርለት እና ልንሞትላት የሚገባ መሆኑን መገንዘብ ወሳኝ ነው፤ ከላይ የተመለከትናቸው አገልጋዮች ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ኅላፊነት አለባቸው፣ ይሄን መፈጸም ያልቻሉ ከመብዛታቸው የተነሳ ወይንም ለእውነት የወገኑ ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው ላለንበት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውጥንቅጥ ምክንያት ዋና ከሆኑ ችግሮቻችን ናቸው ብዬ ለማለት እደፍራለሁ፤ ጳውሎስ ለጤሞቴዎስ አጥብቆ ከሚላቸው ነገሮች መካከል ለእውነት እና ለጤናማ አስተምህሮ ጳውሎስ እንደሚለው “ሕይወት ለሚገኝበት ትምሕርት” እንዲጠነቀቅ ለእንደዚህ አይነት እውነት ጠንክሮ እንዲሰራ ያስጠነቅቀዋል ያበረታታዋልም፤ አሁን ጥያቄው ላለንበት ቀውስ ዋና መነሻው የአገልጋይ እና የአገልግሎት ጥሪ ጤናማነት እጅግ ወሳኝ መሆኑ፤ ልንሄንድበት ልንማር እና ልናድግ የምንችለው እውነት ማእከሉ የሆነ ጉባኤ እና አገልጋይ ባለበት ስፍራ ብቻ ነው፤ እንደነዚህ ያሉ ቦታዎች እምብዛም ተፈላጊነት የላቸውም፣ ብዙ ሰዎች የማይገኙበት ሥፍራ ነው፤
ለቃሉ ትልቅ ስፍራ ያላቸው፣ ክርስቶስ የሚሰበክበት፣ የመስቀሉ እውነት ዋና የሆነበት ስፍራ፤ ልንገኝባቸው የሚገቡ ቤተ ክርስቲያናት አገልጋዮቿ ጳውሎስ በሐሥ 20፥24 “ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።” ለተጠሩለት ትሪ ጥልቅ የሆነ መሰጠት ያላቸው፤ ዋና ሸክማቸው የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል በትክክል ለሌሎች የመድረሱ ጉዳይ ጉዳያቸው የሆነ እንደሆኑ ማየት ይቻላል፤ ምንም እንኳን ዋጋ ቢያስከፍልም (ሞት እንኳን) ቢሆን፤ ፊልጵስዩስ 1:21 “ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው።” በክርስቶስ በሆነው እንገር ላይ በፍጹም መሰጠት ሙሉ ትኩረታቸውን የሰጡ ሰዎች መለያ ምን እንደሚመስል ያሳየናል እንደነዚህ ያሉ አገልጋዮች ያሉበት ስፍራ እንሂድ፤
ምንም እንኳን አገልግሎታቸው የከፋ ዋጋ ቢያስከፍልም ጽናት በትጋት የሚሰሩ እና የሚጋደሉ ናቸው፤ የምናገለግለው አገልግሎት በስተመጨረሻ ዋጋ የሚመዘንለት በማን እንደሆነ ለዚህ ምሳሌ ይሆን ዘንድ ጳውሎስ ለጤሞቴዎስ እንዲህ ይለዋል፤
2 ጢሞቴዎስ 4:7-8
“መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ። ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።” እውነተኛ ጥሪ የሚጠይቀውን ፅናት እና መስዋእትነት እንዲሁም ወንጌሉ ከዚህች ዓለም የሚደርስበትን ተግዳሮቶች የተገነዘቡ እና ይሄንን ለመቋቋም የተሰጡ እንደ እነዚህ አይነት አገልጋዮች ባሉባት አጥቢያ ቃሉን እንገልገል እናገልግልም፤
አገልጋይነታችንንም ሆነ አገልግሎታችንን ሊያሳዩን ከሚያስችሉ ነገሮች መካከል በጥቂቱ ይሄን ይመስላሉ ለጌታ እና ለቃሉ ታማኞች እንድንጎን ሁላችንንም ይርዳን፤